በደቡብ ክልል በአሌ ልዩ ወረዳ ጎሮዜ ቀበሌ ትላንት ማለዳ በ6 ቤቶች ላይ በተከሰተ የመሬት ናዳ ህይወታቸው ያለፈ የ5 ሰዎች አስከሬን መገኘቱ ተገለጸ፡፡
የልዩ ወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ካራ ማሞ እንደገለጹት 6 ቤቶች ከነ ሙሉ ቤተሰቦቻቸው የናዳ አደጋ እንደደረሰባቸዉ አስረድተዋል፡፡

ከሟቾች ውስጥ አንዲት የ3 ሳምንት አራስ እናት ከጨቅላ ልጇ ጋር ህይወቷ አልፎ ተገኝቷል፤ ቀሪ የ7 ሰዎችን አስከሬን የማፈላለግ ስራው እየተከናወነ ነው፡፡
ናዳው ከፍተኛ እንደመሆኑ መጠን ከሰው ጉልበት በተጨማሪ እስካቫተር በመጠቀም አስከሬን ለማፈላለግ ጥረት ቢደረግም አካባቢው ረግረጋማ በመሆኑ ይህን ማከናወን አልተቻለም ይህም የነፍስ አድን ስራውን ፈታኝ እንዳደረገውም ዋና አስተዳዳሪው ጠቁመዋል፡፡
በስጋት ቀጠና ውስጥ የሚገኙ 68 አባወራዎችን መለየት እንደተቻለ የገለጹት ዋና አስተዳዳሪው ከአካባቢው ለተፈናቀሉ ዜጎች መጠለያ ሸራ የማቅረብ ስራ እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል።

የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳው በደረሰው አደጋ ህይወታቸውን ላጡ ዜጎች የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን በራሳቸውና በክልሉ ህዝብ ስም የገለጹ ሲሆን አሁንም ተጨማሪ አደጋ እንዳይከሰት ህብረተሰቡ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበትም ጥሪ ማቅራቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ፅህፈት ቤት ዘግቧል፡፡